የገቢዎች ሚኒስቴር ሚኒስትር ተሾሞለታል (ነሐሴ 13/2014 ዓ.ም)
ነሐሴ 13/2014 ዓ.ም
የገቢዎች ሚኒስቴር ሚኒስትር የነበሩት ክቡር አቶ ላቀ አያሌው በትምህርት ምክንያት ወደውጪ ሀገር ለመሄድ በሚኒስተሮች ምክር ቤት መሸኘታቸውን ተከትሎ ሚኒስቴሩ አዲስ ሚኒስትር ተሾሞለታል፡፡ (ነሐሴ 13/2014 ዓ.ም)
በዚህም መሰረት በወሎ ዩንቨርሲቲ ምክትል ፕሬዘዳንትነት፣ የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ሆነው የሰሩት እና በአማራ ክልል በኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪነት ይሰሩ የነበሩት ክብርት ወ/ሮ ዓይንዓለም ንጉሴ የገቢዎች ሚኒስትር በመሆን የተሾሙ ሲሆን በዛሬው እለት በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የገቢዎች ሚኒስቴር እና የጉምሩክ ኮሚሽን የማኔጅመንት አባላት በተገኙበት የስራ ርክክብ እና የሽኝት ፕሮግራም ተካሂዷል፡፡
የኃላፊነት ርክክብ በተደረገበት ወቅት ክቡር አቶ ላቀ አያሌው ባስተላለፉት መልእክት የገቢዎች ሚኒስቴር ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እና ሰራተኞች በቆይታቸው ስራቸውን እና ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ላገዟቸው ለገቢዎች ሚኒስትር ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች እና ሰራተኞች ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የተደራጀና ሥራቸውን በእውቀት የሚሰሩ የሕዝብ አገልጋዮች የሚገኙበት ከመሆኑም በተጨማሪ በቆይታቸው ለተደረገላቸው ድጋፍ ከፍተኛ ምስጋና እና ክብር እንዳላቸው ገልፀዋል፡፡ ከዚሁ ጋር አያይዘውም ከሰባት ወራት በፊት ለመንግሥት ባቀረብኩት የሥራ መልቀቂያ መሰረት ለአገርና ለሕዝብ ከዚህ የበለጠ ለማገልገል አቅም እንዳገኝ ውጭ አገር የመማር ፈቃድ ስለተሰጠኝ አመሰግናለሁ ብለዋል፡፡
ክቡር አቶ ላቀ በተጨማሪም በ2022 ሀገራችን የራሷን ወጪ በራሷ ገቢ ለመሸፈን የያዘችውን ራእይ ለመሳካት እንዲሁም በ2015 በጀት ዓመት ተቋሙ ከ450 ቢሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ ያቀደውን በብቃት እንዲፈጽም ከፍተኛ የተቋሙ አመራሮች እና ሰራተኞች ከአዲሷ ሚኒስቴር ጎን በመሆን ስራቸውን በኃላፊነት እና በቅንነት መስራት ይጠበቅባችኋል ሲሉ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
በተቋሙ በሚኒስትርነት የተሾሙት ክብርት ወ/ሮ አይናለም ንጉሴ በበኩላቸው ተቋሙ ጠንካራ አደረጃጀት እና የአሰራር ስርዓት ያለው፤ የገቢ አሰባሰብ አፈጻጸሙም በየጊዜው እድገት እያስመዘገበ የሚገኝ እንደመሆኑ ይህንኑ ስኬት ማስቀጠል ብቻ ሳይሆን በ2015 በጀት ዓመት ለመሰብሰብ ከታቀደው በላይ አፈጻጸም ለማስመዝገብ እንዲሁም ሀገራችን እና ህዝባችን የሚጠብቅብንን ለመወጣትም ሁሉም የተቋሙ አመራሮች እና ሰራተኞች ከጎናቸው በመሆን በጋራ እና በትልቅ የኃላፊነት መንፈስ የልማት ወጪን በራሷ መሸፈን የምትችል ሀገር እንድትኖረን ለሚደረገውን ጥረት መረባረብ ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡