የስፖርት ውርርድ /Sport Betting/ መመሪያ ተሻሻለ

የስፖርት ውርርድ ሎተሪን ጥብቅ በሆነ ሕግና ስርዓት እንዲመራ ማድረግና ቁጥጥሩን ለማጠናከር፤ ቀደም ሲል በነበረው መመሪያ ያልተካተቱ ተጨማሪ ክልከላዎች ማካተት በማስፈለጉ፤ የአዲስ ፈቃድ ማውጫ፣የፈቃድ እድሳት ክፍያና የማህበራዊ አገልግሎት ክፍያ ማሻሻል በማስፈለጉ እንዲሁም የዓለም የስፖርት ውርርድ ሎተሪ ህጎች ከደረሰቡት የእድገት ደረጃ ጋር ተቀራራቢ ለማድረግና በአወራራጁና በተወራራጁ መካከል የሚነሱ አለመግባባቶችን ለመፍታት የሚያስችል መመሪያ ማዘጋጀት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ አዲስ መመሪያ ተዘጋጅቷል፡፡

የገቢዎች ሚኒስቴር የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደርን እንደገና ለማቋቋም በወጣው የሚኒስትሮች ምክርቤት ደንብ ቁጥር160/2001 አንቀጽ 21 በተሰጠው ሥልጣን መሰረት የስፖርት ውርርድ ሎተሪ ፈቃድ መመሪያ ቁጥር 83/2005 በዚህ መመሪያ አሻሽሏል፡፡ በዚህም መሰረት የሎተሪ ፈቃድ መመሪያን ለማሻሻል የወጣ መመርያ ቁጥር 172/2013 ወጥቶ ተግባራዊ ሆኗል፡፡

ለዛሬ በዚህ ሥራ ላይ የተሰማሩ አወራራጆች ጠቅላላ ግዴታዎችና ኃላፊነቶች ምን ምን እንደሆኑ ከሚተለው መረጃ መገንዘብ ይችላሉ፡-

1. ማናቸውም በስፖርት ውርርድ ሎተሪ ጨዋታ አሸናፊ ሆነው ለቀረቡ ዕድለኞች ክፍያ በህጋዊ ደረሰኝ መፈፀም አለበት፡፡

2. የጨዋታው አሸናፊ አሸናፊነቱ ታውቆ ከቀረበበት ቀን ጀምሮ እስከ 15 ቀናት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ሽልማቱን የመስጠት ግዴታ አለበት፡፡

3. ከዕድል ሙከራ ከተገኘ ገቢ 15%ኮሚሽንና ከዕድለኞች የሚቀነስ 15%የገቢ ግብር ክፍያ ለአስተዳደሩ በየወሩ መክፈል አለበት፡፡

4. አንድ የአሸናፊ ቲኬት ዋጋ የሚኖረው 30 ቀናት ብቻ ነው፡፡

5. ማንኛውም ባለፈቃድ የአሸናፊ ቲኬት ዋጋ የሚኖረው 30 ቀናት ብቻ ነው የሚል መልእክት ለደንበኛው በሚሸጠው ትኬት ላይ ወይም በሌላ መንገድ መግለጽ አለበት፡፡

6. የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደሩን ኮሚሽን ክፍያ፣ የበጎ አድራጎት ክፍያ፣ የገቢ ግብር ክፍያ እና የአሸናፊ የዋስትና ክፍያ ለማስጠበቅ በቅድመ ሁኔታ ያልተመሠረተ የባንክ ዋስትና ብር 1,500,000.00 /አንድ ሚሊየን አምስት መቶ ብር / ማቅረብ አለበት፡፡

7. ባለፈቃዱ በአንድ የስፖርት ውርርድ ጨዋታ ለአንድ የውርርድ ተጫዋች መክፈል የሚችለው ከፍተኛው የሽልማት ጣርያ ከብር 1,000,000.00 /አንድ ሚሊየን ብር/ መብለጥ የለበትም፡፡

8. ባለፈቃዱ ቅርንጫፍ ሲከፍት ወይም ሲዘጋ ለብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ወዲያውኑ ማሳወቅ አለበት፡፡

9. ድርጅቱ የይለፍ ቁጥር (የሲስተም አክሰስ ኮድ) አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ የመስጠት ግዴታ አለበት፡፡

10. የስፖርት ውርርድ ሎተሪ የሚካሄድበት የስፖርት ጨዋታ በተለያየ ምክንያት ባይካሄድ፣ ቢቋረጥ፣ ቢሰረዝ ደንበኛው የተወራረደበት ጨዋታ አንድ ከሆነ ገንዘቡ መመለስ አለበት፡፡

11. ተወራራጁ ያስያዛቸው ጨዋታዎች ከአንድ በላይ ከሆኑ ያልተካሄዱት የተሰረዙ ጨዋታዎች ወጥተው ውጤቱ በተቀሩት ጨዋታዎች ይወሰናል፡፡

12. አወራራጁ በማንኛውም ጨዋታ ለደንበኛው ትኬት ቆርጦ ከሰጠ በኋላ ደንበኛው ያሸነፈበትን ትኬት ይዞ ሲቀርብ ሌላ የተለየ ችግር ከሌለ በስተቀር ክፍያ ላለመፈፀም የሲስተም ችግር ነው የሚል ምክንያት ተቀባይነት አይኖረውም፡፡

13. የሂሳብና ሌሎች ሰነዶች በአስተዳደሩ በተጠየቀ በማናቸውም ጊዜ የማቅረብ ግዴታ አለበት፡፡

14. የስፖርት ውርርድ ሎተሪ በሚካሄድበት ቦታ ማንኛውንም ሌሎች የዕድል ሙከራ ጨዋታዎችን እንዳይካሄድ የማድረግ ኃላፊነት አለበት፡፡

.

በብዛት የተነበቡ ዜናዎች

  • "ከፍተኛ ግብር ከፋዮች የታክስ ህግን በማክበርና የልዕቀት ማዕከል በመሆን አርአያ ሊሆኑ ይገባል" የገቢዎች ሚኒስትር አቶ ላቀ አያሌው Fri, 29 Oct 2021
"ከፍተኛ ግብር ከፋዮች የታክስ ህግን በማክበርና የልዕቀት ማዕከል በመሆን አርአያ ሊሆኑ ይገባል" የገቢዎች ሚኒስትር አቶ ላቀ አያሌው
  • "የሀገራችንን ኢኮኖሚ በጽኑ መሰረት ላይ ለማቆም በሚደረገው ጥረት የገቢዎች ሚኒስቴር እና የጉምሩክ ኮሚሽን ያላቸው ድርሻ ከፍተኛ በመሆኑ ለአፍታም ቢሆን ሳናሸልብ ተግተን እንሰራለን " ወ/ሮ አይናለም ንጉሴ (የገቢዎች ሚኒስትር) Wed, 4 Jan 2023
"የሀገራችንን ኢኮኖሚ በጽኑ መሰረት ላይ ለማቆም በሚደረገው ጥረት የገቢዎች ሚኒስቴር እና የጉምሩክ ኮሚሽን ያላቸው ድርሻ ከፍተኛ በመሆኑ ለአፍታም ቢሆን ሳናሸልብ ተግተን እንሰራለን " ወ/ሮ አይናለም ንጉሴ (የገቢዎች ሚኒስትር)