ከግብር እና ታክስ ስወራ ጋር ተያይዞ ለተጨባጭ መረጃ አቅራቢ ስለሚሰጥ ሽልማት

Posted in Know How

ማህበራዊ፣ ኢኮሚያዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ተገቢው ውጤት እንዲያመጡ ከተፈለገ ህብረተሰቡን ማሳተፍ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር መሆን ይኖርበታል፡፡የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣንም ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ በብቃት ለመሰብሰብ፣ለልማታችንና ለልማታዊ ባለሀብቱ ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር እንዲሁም ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል እንዲኖር የሚያደርገውን ጥረት ለማስቀጠል ህብረተሰቡን የሚያሳትፉ እቅዶችን በማዘጋጀት እየሰራ ነው፡፡በመሆኑም ግብር ከፋዩ ማህበረሰብና ባለስልጣ በበርካታ ጉዳዮች ላይ በጋራ እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ኮንትሮባንድ፣ ህገ-ወጥ ንግድ እና ታክስ ማጭበርበርን ለመከላከል በእነዚህ ተግባራት ላይ የተሰማሩትን በመታገል ማህበረሰቡ እያበረከተ ያለው አስተዋፅኦ ጉልህ ነው፡፡ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የህብረተሰቡን ተሳትፎ ለማሳደግ የሚያስችሉ የተለያዩ መመሪያዎችን በማውጣት ተግባራዊ አድርጓል፡፡ በዚህም  የህገ-ወጥ እቃዎችን እንቅስቃሴ የመከላከልና የመቆጣጠር ስራ ውስብስብ በመሆኑ እና ድርጊቱም በተሻለ ሁኔታ ለመከላከልና ለመቆጣጠር የህብረተሰቡን ተሳትፎ ማሳደግ አስፈላጊ ነው፡፡ ኮንትሮባንድ፣ የንግድ ማጭበርበር፣ የተከለከሉ ወይም ገደብ ከተደረገባቸው እቃዎች ጋር በተያያዘ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ከጊዜ ወደ ጊዜ በይዘትም ሆነ በመጠን እየተበራከቱና እየተወሳሰቡ በመሄዳቸው በገበያው ወይም በህጋዊ ንግዱ እንቅስቃሴ፣ በመንግስት ገቢ አሰባሰብ እንዲሁም በህብረተሰቡ ደህንነት ላይ ከፍተኛ አደጋ የሚጥሉ በመሆናቸው፤ እነዚህን አገራዊ አደጋዎች ለመቆጣጠር እና ለመከላከል የሚያስችል ስልቶች ተዘርግተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን በጉምሩከ አዋጅ ቁጥር 859/2006 በተሰጠው ስልጣን መሰረት የጉምሩክ ህጎችን በመተላለፍ የሚፈጸሙ ጥፋቶችን የመከላከል፣ የመመርመርና በጥፋተኞች ላይ አግባብነት ያለው እርምጃ የመውሰድ ወይም የማስወሰድ ተግባራትን ያከናውናል፡፡ በተጨማሪም ሌሎች ከግብር እና ታክስ ጋር ተያይዞ የሚፈጸሙ ስወራ ወይም ማጭበርበሮችን ለመከላከል ህብረተሰቡን የሚያሳትፉ ስራዎችን ይሰራል፡፡

የግብር እና ታክስ ስወራ ወይም ማጭበርበር መገለጫዎች

በማንኛውም መረጃ አቅራቢ መረጃ የሚቀርብባቸው የግብር/ታክስ ስወራና ማጭበርበር ድርጊት መገለጫዎች

በታክስ ህግ መሰረት ግብር እና ታክስ የመሰወር ወይም የማጭበርበር ድርጊት ተብለው የተደነገጉ ማናቸውንም የህግ ጥሰት ድርጊቶች እና

ታክስ ከፋዩ የታክስ ህግ ጥሰት መፈጸሙን፣ ግብር የሚከፈልበት ገቢ ወይም ታክስ መደበቁን፣ ገቢ በማሳነስና ባለማስታወቅ ግብር እና  ታክስ መሰወሩን፣ ወጪን በማናር ወይም በሌላ ማናቸውም መንገድ በማጭበርበር ግብር ግብር/ታክስ አለመክፈሉን፣ የማይገባውንተመላሽ መጠየቁን ወይም መውሰዱን የሚያመላክቱ ድርጊቶችን ያጠቃልላል፡፡ 

በባለስልጣኑ ሊመዘገብና ሊጣራ የሚችል ተቀባይነት ያለው መረጃ

ማናኛውም መረጃ አቅራቢ ለባለስልጣኑ የሚያቀርበው መረጃ ተቀባይነት ያለው መረጃ እንደሆነ ተቆጥሮ የሚመዘገበው፡-

መረጃ አቅራቢው በፈቃደኝነት ያቀረበው መረጃ ሲሆን፤

የታክስ ህግ ጥሰት መፈጸሙን የሚያመላክት መገለጫ የያዘ መረጃ ሲሆን፤

የመረጃ ምንጩ በዚህ መመሪያ አንቀጽ 6 የተዘረዘሩትን መረጃን ውድቅ የሚያስደርጉ የመረጃ ምንጮች ሳይጨምር ከማንኛውም ሌላ     ሶስተኛ ወገን የተገኘ   መረጃ ሲሆን፤ 

መረጃ አቅራቢው በራሱ ጥረት፣ ክትትል፣ ትንተናና ጥናት የደረሰበት አዲስ (ኦሪጅናል) መረጃ ሲሆን፤መረጃው ከመቅረቡ በፊት ባለስልጣኑ በራሱ ያልደረሰበት ወይም ባለስልጣኑ ቀደም ብሎ ኦዲት ለማድረግ በያዘው ዝርዝር ውስጥ ያልተካተተ ሲሆን፤

ባለስልጣኑ ቀደም ብሎ ደርሶበት በኦዲት ተጣርቶ ለታክስ ከፋዩ ውሳኔ ከደረሰው በኋላ ወይም የማጣራት እና የኦዲት ሥራ ከተጀመረ በኋላ መረጃ አቅራቢው በባለስልጣኑ ሊደረስበት የማይችል የተሸፈነ ወይም የተሸሸገ መረጃ ወይም ሚስጥር የያዘ መረጃ የሰጠ ሲሆን፤

ባለስልጣኑ በማንኛውም ሌላ መንገድ ሊደረስበት የማይችል መረጃ ሆኖ ከተገኘ፤

አቅራቢው በፈቃደኝነት ያቀረበው መረጃ እንደሆነ የሚቆጠረው ባለስልጣኑ ወይም ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት በአወሳሰን፣ በኦዲት፣ በምርመራ፣    በተመሰከረላቸው የሂሳብ እና የኢዲት ድርጅቶች የሚፈለግ መረጃ እንዲሰጥ ለመረጃው አቅራቢው ጥያቄ የቀረበለት ከሆነ ጥያቄው ከመቅረቡ በፊት የሰጠው መረጃ ሲሆን ብቻ ነው፡፡

መረጃው በይሆናል፤ በትንበያ፤ በግምት ወይም በጅምላ ያልቀረበ ሆኖ አቀራረቡ ግልፅ፤ የማያሻማ፤ ተአማኒነት ያለው፤ በግብር ዓመት፤ በታክስ ዓይነት፤ በመጠን ተለይቶ የቀረበ፤ ሊጣራ እና ሊረጋገጥ የሚችል እና ገቢ የሚሰበሰብበት መሆን አለበት፤

በባለስልጣኑ ሊመዘገብ እና ሊጣራ የማይችል ተቀባይነት የሌለው መረጃ

ማንኛውም መረጃ አቅራቢ ለባለስልጣኑ የሚያቀርበው መረጃ ተቀባይነት የሌለው መረጃ እንደሆነ ተቆጥሮ ውድቅ የሚያደርገው፡-

የመረጃ ምንጩ ከፍርድ ቤት ክርክር ወይም ውሳኔ፣ ከመንግስት ሪፖርት፣ ከአቤቱታ፣ ከኦዲት ስራ፣ ለሚድያ እና ከመሳሰሉት ሌሎች የህትመት ምንጮች የተገኘ ወይም በማንኛውም መንገድ በሌላ ሶስተኛ ወገን የቀረበ ከሆነ፤

መረጃ አቅራቢው ያቀረበው መረጃ ምንጩ በሙያቸው ሪፖርት የማድረግ ግዴታ በህግ ከተጣለባቸው የተመሰከረላቸው የሂሳብ አዋቂዎች፣ የኦዲት ድርጅቶች እና ባለሙያዎች፣ ከታክስ ከፍዩ የህግ አማካሪ፣ የንግድ እንደራሴ፣ የሂሳብ ባለሙያዎች እና ኦዲተሮች ያገኘው መረጃ ከሆነ፤

በህግ ለሽልማት ብቁ ስላለመሆን ተብለው ከተዘረዘሩት ሰዎች ወይም ከእነርሱ ቤተሰቦች የተገኘ መረጃ ከሆነ፤

ለሽልማት የቀረበው መረጃ ቀደም ብሎ በሌላ መረጃ አቅራቢ የቀረበ ከሆነ፤

  መረጃው ከመቅረቡ በፊት ባለስልጣኑ በራሱ የደረሰበት ወይም ባለስልጣኑ ቀደም ብሎ ኦዲት ለማድረግ በያዘው ዝርዝር ዕቅድ ውስጥ የያዘው ከሆነ፤

  ባለስልጣኑ ሽልማት ከመሰጠቱ በፊት በማናቸውም ጊዜ ሁኔታውን ያወቀ ከሆነ ነው፡፡ ስለሆነም ተቀባይነት የሌለው መረጃ ሆኖ ከተገኘ መረጃው ውድቅ ተደርጎ ይህንኑ ለመረጃ አቅራቢው እንዲያውቀው በአምስት የስራ ቀናት ውስጥ በፅሁፍ መግለፅ አለበት፤

መረጃ የሚቀርብባቸው መንገዶች  

የግብርና ታክስ ስወራ መረጃ በግንባር፤ በፖስታ፤ በስልክ፤ በኢ-ሜል ወይም አመቺ በሆነ በማንኛውም ሌላ መንገድ በየደረጃው ላሉ የባለስልጣኑ ኢንተለጀንስ የመረጃ አቀባበል እና ምዝገባ የሰራ ክፍል በማቅረብ፤

መረጃ ሰጪው በየደረጃው ላሉ የባለስልጣኑ ኢንተለጀንስ የመረጃ አቀባበል እና ምዝገባ የስራ ክፍል መረጃ ማቅረብ ካልቻለ ለባለስልጣኑ ሌላ የስራ ክፍል ወይም ለሌሎች የሚመለከታቸው የፌደራልና የክልል የመንግስት መስሪያ ቤቶችና ህግ አስከባሪ አካላት መረጃ መስጠት ይቻላል፤

መረጃ የቀረበበት የባለስልጣኑ ሌላ የስራ ክፍል የቀረበለትን መረጃ ወዲያውኑ፤ ሌሎች ከባለስልጣኑ ውጭ ጥቆማ ወይም መረጃ የተቀበሉ የፌደራል ወይም  የክልል መስሪያ ቤቶች እና የህግ አስከባሪ አካላት ደግሞ መረጃውን በአርባ ስምንት ሰዓት ውስጥ በየደረጃው ላሉ የባለስልጣኑ ኢንተለጀንስ የመረጃ አቀባበል እና አመዘጋገብ የስራ ክፍል ማቅረብ አለባቸው፡፡

በህግ መሰረት ለሽልማት ብቁ ስላለመሆን

በባለስልጣኑ ተቀባይነት ያገኘ ተጨባጭ መረጃ በሚከተሉት የቀረበ ከሆነ መረጃ አቅራቢ ለሽልማት ብቁ አይሆንም፡፡

  የታክስ ስወራን ማሳወቅ የመደበኛ ስራው አካል የሆነ ሰው፤

በፌደራል ወይም በክልል መንግስታዊ መ/ቤቶች ወይም በእነዚህ አካላት የሚሰሩ ሰራተኞች በስራ ኃላፊነታቸው ምክንያት ባገኙት መረጃ መነሻነት የቀረበ ከሆነ፤

የግብር/ታክስ ስወራን ወይም ማጭበርበርን በማቀድ ውሳኔ በመስጠት በመሳሰሉት ድርጊት ተካፋይ በሆነ ሰው የቀረበ ከሆነ፤

  በባለስልጣኑ ሰራተኞች ወይም ተሿሚዎች ወይም በቤተሰባቸው የቀረበ ከሆነ፤

  የባለስልጣኑ የቀድሞ ሰራተኛ በሰራ ኃላፊነቱ ምክንያት መረጃ ከሰበሰበበት ወይም ከመረመረው ወይም ኦዲት ካደረገው ጋር በተያያዘ ጉዳይ ላይ በራሱ ወይም በቤተሰቡ አማካኝነት መረጃ ማቅረቡ ከተረጋገጠ፤

የታክስ ስወራ ወይም ማጭበርበር መፈፀም ሲያውቁ ሪፖርት የማድረግ ግዴታ የተጣለባቸው የተመሰከረላቸው ሂሳብ አዋቂዎች የውስጥና የውጪ ኦዲተሮች የሂሳብ ሰራተኞች እና ሌሎች፤

መረጃ አቅራቢው መረጃውን ስለማቅረቡ በባለስልጣኑ የተሰጠውን ማስረጃ ካላቀረበ ለሽልማት ብቁ አይሆንም፤ ሆኖም ከአቅም በላይ የሆነ ችግር ያጋጠመው መሆኑ ከተረጋገጠ ባለስልጣኑ በማስረጃው ከሌሎች ስራ ክፍሎች ጋር ያቀረበውን መረጃ በሚመለከት ግንኙነት ማድረጉ ከተደረሰበት፤

ከዚህ በላይ ከተዘረዘሩት ለሽልማት ብቁ ካልሆኑ ሰዎች ወይም ቤተሰቦቻቸው በእጅ አዙር መረጃ አግኝቶ ለባለስልጣኑ መረጃ ያቀረበ ማንኛውም መረጃ አቅራቢ፤

  በሌሎች የፌደራል ወይም የክልል መንግስታዊ መ/ቤቶች የሚሰሩ ሰራተኞች ከስራ ኃላፊነታቸው ውጪ በራሳቸው ጥረት ያገኙትን መረጃ በራሳቸው በማቅረብ ሽልማት ለማግኘት ይችላሉ፡፡ እንዲሁም እነዚህን ሠራተኞች የመረጃ ምንጭ በማድረግ አጥንቶ እና የራሱን ጥረት አድርጎ መረጃ ያቀረበ ማንኛውም መረጃ አቅራቢ ለሽልማት ብቁ ሆኖ መሸለም ይችላል፤

  ኪሳራ በማያሳውቁ ድርጅቶች ላይ በሚቀርብ መረጃ ኪሳራ በመሸጋገሩ ምክንያት ትርፍ ካልተገኘ በስተቀር በሽልማት ብቁ አያደርግም ሽልማትም አያስገኝም፡፡

የመክፈያ ጊዜ

ለተመዘገበ መረጃ ሽልማት የሚከፈለው መረጃው በባለስልጣኑ ኦዲተሮች ተመርምሮ ተጨባጭ መረጃ መሆኑ ተረጋግጦ ገቢው ወይም ታክሱ ሲሰበሰብ፤

ግብር ከፋዩ ታክሱን በአንድ ጊዜ ሳይሆን በጊዜ ስምምነት አከፋፍሎ እንዲከፍል ባለስልጣኑ ሲፈቅድ እና ውል ሲገባ በየመክፈያው ጊዜው ድርሻው ከተሰበሰበሰው እየተሰላ፤

  በፍርድ ቤት ክርክር የቀረበበት የኢንቨስቲጌሽን ኦዲት ግኝት እና ውሳኔ ከሆነ የፍርድ ቤት የመጨረሻ ውሳኔ ማግኘቱ እና ገቢው መሰብሰቡ ሲረጋገጥ መሆን አለበት፤

  ስለሆነም በማናቸውም ሁኔታ መረጃ የቀረበበት እና በኦዲተሮች ግኝት የተረጋገጠ ገቢ ወይም ታክስ ሳይሰበሰብ የሽልማት ክፍያ መክፈል የተከለከለ ነው፡፡

የሽልማት ክፍያ የሚፈጸመው

  የሽልማቱ መጠን የሚሰላው በተሰጠው መረጃ መሰረት በተገኘው ገቢ ወይም ታክስ ላይ ተመስርቶ ግኝቱ መረጃ በቀረበበት ዘመን እና የታክስ ዓይነት ከተለየ በኋላ በመቶኛ እተሰላ ይሆናል፤

የገቢ ግብር ሲሆን ለሽልማቱ ስሌት መሰረት የሚደረገው መረጃው ባይቀርብ ኖሮ ተሰውሮ ወይም ተጭበርብሮ ሊቀር በነበረው ፍሬ ግብር መጠን እና ወለድ ላይ፤

በማንኛውም የታክስ ህግ መሰረት ተሰብስቦ ገቢ መደረግ ያለበት ታክስ ሲሆን መረጃው ባይቀርብ ኖሮ ተሰውሮ ወይም ተጭበርብሮ ሊቀር በነበረው ታክስ መጠን እና ወለድ ላይ፤

  የቀረበው መረጀ ገቢ ግብርን እና ታክስን ያካተተ ሆኖ በኦዲት ተመርምሮ የተረጋገጠውም ይሄው ከሆነ የሽልማቱ መሰረት የሚሆነው ገቢ ግብሩ እና ታክሱ ለየብቻ ተለይቶ በማስላት፤

ለመረጃ አቅራቢው የሚሰጠው ሽልማት በተሟላ መንገድ ዝርዝር መረጃ በሰጠበት የግብር ዘመን እና የታክስ ዓይነት ከተገኘው ገቢ ላይ እና

ኦዲት የተደረገው ግብር ወይም ታክስ በቀረበው መረጃ መነሻ ሆኖ መረጃ ከቀረበበት ጭብጥ እና የታክስ ዘመን በላይ የሚሸፍን ከሆነ ለመረጃ አቅራቢው  የሚሰጠው ሽልማት መረጃ የቀረበበት የታክስ ዘመን ግኝት ላይ ብቻ ይሆናል፡፡

የሽልማት ምጣኔ ደረጃ

  በተጨባጭ መረጃው መሰረት የተገኘው ፍሬ ግብር/ታክስ እና ወለድ መጠን

  ከዝቅተኛው መጠን እስከ 60,000,000 (ስድሳ ሚሊዮን ብር) ከሆነ 5%፤

  ከብር 60,000,001 (ስድሳ ሚሊዮን አንድ) እስከ ብር 70,000,000 (ሰባ ሚሊዮን) ከሆነ 6%፤

  ከብር 70,000,001 (ሰባ ሚሊዮን አንድ) እስከ ብር 80,000,000 (ሰማኒያ ሚሊዮን) ከሆነ 7%፤

  ከብር 80,000,001 (ሰማኒያ ሚሊዮን አንድ) እስከ ብር 90,000,000 (ዘጠና ሚሊዮን) ከሆነ 8%፤

  ከብር 90,000,001 (ዘጠኝ ሚሊዮን አንድ) እስከ ብር 100,000,000 (አንድ መቶ ሚሊዮን) ከሆነ 9%፤

  ከብር 100,000,001 (አንድ መቶ ሚሊዮን አንድ) እስከ ብር 110,000,000 (አንድ መቶ አስር ሚሊዮን) ከሆነ 10%፤

   ከብር 110,000,001 (አንድ መቶ አስር ሚሊዮን አንድ) እስከ ብር 120,000,000 (አንድ መቶ ሃያ ሚሊዮን) ከሆነ 11%፤

   ከብር 120,000,001 (አንድ መቶ ሃያ ሚሊዮን አንድ) እስከ ብር 130,000,000 (አንድ መቶ ሰላሳ ሚሊዮን) ከሆነ 12%፤

  ከብር 130,000,001 (አንድ መቶ ሰላሳ ሚሊዮን አንድ) እስከ ብር 140,000,000 (አንድ መቶ አርባ ሚሊዮን) ከሆነ 13%፤

  ከብር 140,000,001 (አንድ መቶ አርባ ሚሊዮን አንድ) እስከ ብር 150,000,000 (አንድ መቶ ሃምሳ ሚሊዮን) ከሆነ 14%፤

  ከብር 150,000,001 (አንድ መቶ ሃምሳ ሚሊዮን) በላይ ከሆነ 14% ሆኖ በማንኛውም ሁኔታ ለተሸላሚ የሚከፈለው የወሮታ ክፍያ ከብር 30,000,000 (ሰላሳ ሚሊዮን) መብለጥ የለበትም፡፡ 

 የሽልማት ክፍያ ግብር የሚከፈልበት ስለመሆኑ

በዚህመመሪያ መሰረት የሚከፈል ሽልማት በገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 979/08 መሰረት ግብር ይከፈልበታል፡፡ ስለሆነም ሽልማት የሚከፍል የባለስልጣኑ የሥራ ክፍል ክፍያ ሲፈጽም ግብሩን ቀንሶ ማስቀረት አለበት፡፡

ሽልማት ተመላሽ ስለማድረግ

            ባለስልጣኑበማናቸውም ሁኔታ በስህተት ወይም ያለአግባብ የከፈለውን ሽልማት እንዲመለስ ያደርጋል፡፡       

Visitors: Yesterday 38 | This week 229 | This month 285 | Total 431139

We have 257 guests and no members online